የኪነ ጥበብ ዕድገትን የሚያሳልጡና የአይችሉም ታ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የኪነ ጥበብ ዕድገትን የሚያሳልጡና የአይችሉም ታሪክን የቀየሩ በርካታ የለውጥ መሰረቶች እየተገነቡ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የሁለንተናዊ ብልፅግና ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነውን የኪነ ጥበብን ዕድገትየሚያሳልጡና የአይችሉም ታሪክን የቀየሩ የለውጥ መሰረቶች እየተገነቡ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎችም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አስተዳደሩ ያስገነባዉን ዘመናዊ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ኮምፕሌክስን መርቀዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ለኪነ ጥበብ ዕድገት ብቻ ሳይሆን የአይችሉም ታሪክን የቀየሩ የለውጥ መሰረቶች እየተገነቡ ነው።

ኪነ ጥበብ ሀገር ስትለማ አወድሳ ለትውልድ የምታሰርፀውን ያህል ሳይሰራ ሲቀር በእንጉርጉሮ ቁጭትን የመፍጠር አቅሟ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ኪነ ጥበብ መሠል ሚናዋን በአግባቡ እንድትወጣ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ኪነ ጥበብ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር እንደሆነች መንግስት ፅኑ እምነት እንዳለው ጠቁመው፤ ኪነ ጥበብ የትናንት፣ የዛሬንና የነገን ትውልድ በማስተሳሰር ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳላት አብራርተዋል።

የኪነ ጥበብ ታሪክ ሲወሳ አዲስ አበባ የአንበሳውን ድርሻ ትወስዳለች ያሉት ከንቲባ አዳነች የኪነ ጥበብ ዕድገት የዘመኑን ያህል አይደለም ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት  የለውጥ ዓመታት አዲስ አበባ ከተማ በፈጣን የለውጥ ጉዞ ላይ እንደምትገኝ አመልክተው፤ ለነዋሪዎች ምቹ ለኪነ ጥበብ ደግሞ ዘመኑን የዋጀ የመከወኛ ሥፍራ እየሆነች መምጣቷንም አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ነባር ቴአትር ቤቶችን በማደስ እና በርካታ አዳዲስ የቴአትር ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።

የጥበብ ሥራ በአዳራሽ ብቻ የታጠረ አለመሆኑን ታሳቢ በማድረግ በከተማዋ 110 ፕላዛዎችና ከ50 በላይ አምፊ ቴአትሮች መገንባታቸውን ተናግረዋል።

ዛሬ የተመረቀው የቴአትር ኮምፕሌክስ ሁለት ባለ 14 ወለል ብሎኮችን፣ 1 ሺህ 200 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው አንድ ቴአትር እና ሁለት ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶች እንዲሁም ልዩ ልዩ መገልገያዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።

የቴአትር ኮምፕሌክሱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና አዲስ አበባን የሚመጥን መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከንቲባዋ ከተማ አስተዳደሩ ለኪነ ጥበብ ዕድገት ሁለንተናዊ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አረጋግጠው፤ ከያንያን ሚናቸውን ለትውልድና ለሀገር ግንባታ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.