ኢሬቻ ለአብሮነት ፤ ለወንድማማችነት! Irreec...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ኢሬቻ ለአብሮነት ፤ ለወንድማማችነት! Irreechi Obbolummaaf!

በየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር 'ኢሬቻ ለወንድማማችነት' በሚል መሪ ሀሳብ ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብር ተካሄደ!

የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ደማቅ ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ ላይ አካሄዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፣ የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍፁም ኃይሌ፣ የክፍለ ከተማው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መገርሳ ገላና፣ የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው አስራት፣ የከተማ ደጋፊ ከፍተኛ አመራሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የቀድሞ የባህር ኃይል አባላት፣ የስፖርት ቤተሰቦችን ጨምሮ የክፍለና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ከ12ቱ ወረዳዎች የተወጣጡ የስፖርት ማህበረሰብ ተሳትፈዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ለተሳታፊዎች እንደገለፁት በከተማችን አዲስ አበባ የ2018 የደመራና መስቀል በዓልን ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ አክብረን በቀጣይ በድምቀት የሚከበረውን የአብሮነትና የፍቅር መገለጫ የኢሬቻ በዓልንም በተሳካ ሁኔታና በሰላም እንዲከበር ከመላው ነዋሪዎቻችን ጋር በቅንጅትና በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አቶ በላይ አክለውም ኢሬቻ የአንድነት፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት በዓል ከመሆኑም በላይ የእርስ በርስ ግንኙነታችንን ለማጠናከር ያለው ሚና የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ኃይሌ በበኩላቸው አዲስ አበባ በፍጥነት እየተለወጠች ያለች እና የቱሪስት መዳረሻነቷ እየጎላ የመጣ ከተማ በመሆኗ በመጪው ሳምንት በድምቀት በምናከብረው በኢሬቻ በዓል ላይም እንግዳ ተቀባይነታችንን በማጎልበት የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በተካሄደው ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ የከተማና የክፍለ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክፍለ ከተማውና የወረዳ የስፖርት ማህበረሰብ ተሳታፊዎች በጋራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ለመጪው የኢሬቻ በዓል ያለውን ቅድመ ዝግጅት እና የጋራ አብሮነት መልዕክት አስተላልፈዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.