.png)
ለአንድ ሀገር ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ወጥና ተናባቢ የመረጃ ስርዓት መኖር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለዉ ወሳኝና ቁልፍ ጉዳይ ነዉ።
ዉይይቱ በኢትዮጽያ ስታትስቲክስ የልማት ፕሮግራም፣በክልል ኢኮኖሚ አካዉንት ፣በዲጂታል የእቅድ ክትትልና ግምገማ ስርዓት እንዲሁም በመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ላይ ያተኮረ እንደነበረ ታውቋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚንስተር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) እንደገለፁት በእነዚህ አራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በአዋጅ በተሠጠዉ ስልጣንና ኃላፊነት እስከአሁን እንደ ክልል ብሎም እንደ ከተማ ጥናቶች መደረጋቸዉንና ግብዓትንና ስልጠናን ያካተቱ ተግባራት በሰፊዉ ትኩረት ተሠጥቶባቸዉ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
አያይዘዉም ሚንስተር መስሪያ ቤቱ በአተገባበር ወቅት እንደክልልም ሆነ እንደከተማ የመጡ ስኬቶች፣ የታዩ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ለከተማዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች የጥናት ዉጤቶች ያቀረበበትና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያካተተ የጋራ ልምድና ተሞክሮ የተወሠደበት ዉይይት ነዉ ብለዋል።
በዚህ መነሻነትም መዲናችን እንደክልልም ሆነ እንደ ከተማ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ወጥና ተናባቢ የመረጃ ስርዓት እንዲኖራት በምናደርገዉ የጋራ ርብርብ ለፖሊሲ ጥናትና ለዉሳኔ አሰጣጥ አጋዥ የሆኑ ጅምር ስራዎችን ማጠናከር ይገበል ያሉት ሚንስተሯ ለዚህም ዉይይቱ የጋራ አቋም ይዘን በበጀት ዓመቱ የበለጠ በሙሉ አቅም ወደ ተግባር ለመግባት አቅም የፈጠረ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል።
በግብርና ቆጠራ፣በኢኮኖሚ ድርጅት ቆጠራ፣ በማህበራዊ ዘርፍ ጉዳዮች እና በተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከተማዋ ለጀመረችዉ ሁለተናዊ እድገትም ሆነ እንደ ሀገር ያለዉ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ሚንስተሯ በሰጡት ማብራሪያ ገልፀዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሪድዋን በበኩላቸዉ የዛሬዉ ዉይይት ዓላማ በአራቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ሚንስተር መ/ቤቱ ጥናትን መሠረት አድርጎ ያከናወናቸዉን ዝርዝር ተግባራት ከከተማችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ከከተማ እስከ ሀገር አቀፍ ወጥ የሆነ ተነባቢ የመረጃ ስርዓት ለመዘርጋት ያለመ ነዉ ብለዋል ።
አክለዉም ዓለም አቀፋዊ ደረጃን የጠበቀ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ወጥነት ያለዉ የመረጃ ስርዓት መኖር ዉጤታማ የእቅድ ዝግጅትና አፈፃፀም እንዲኖር፣ ግልፅና ሊተገበር የሚችል ፖሊሲዎችን ለመቅረፅ፣በመረጃ የተደገፈ ተጨባጭ ዉሳኔዎችን ለመወሰን፣ተቋማት ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ፈጣን እና ትክክለኛ መረጃዎችን ለመለዋወጥ እና ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በእነዚህ መሠረታዊ የሆኑ ከተማ አቀፍ፣ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ዉጤት የታየባቸዉ በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን እና ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የገለፁት አቶ አብዱልቃድር ሪድዋን በዛሬዉ ዉይይት የተገኙትን ልምዶች በመዉሠድ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም የታለመዉን ግብ በጋራ የበለጠ ለማሳካት ከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኛ መሆኑን በሠጡት ማብራሪያ አመላክተዋል።
በመጨረሻም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያደረገዉን ጥረት በማድነቅ በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.