.png)
የፀጥታ አካላት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በተሳካ መልኩ እንዲከበሩ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀው ወደ ተግባር መግባታቸው ተገለጸ፡፡
የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በተሳካና በሠላም ለማክበር በሚቻልበት ዝርዝር ጉዳየች ከሀገር መከላከያ፣ ከፌዴራል፣ ከአዲስ አበባ እና ከኦሮሚያ ሸገር ከተማ ፖሊስ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ሠላም አዳራሽ ውይይት ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፈንታ አዲስ ዓመት ከመግባቱ አስቀድሞ በነበሩ ሳምንታት ሀገራችን ያስተናገደቻቸው በአዲስ አበባ የተካሄዱ ልዩ ልዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች፣ በጳጉሜ ወር የተከበሩ ቀናቶች እንዲሁም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምረቃ አስመልክቶ የተካሄዱ የደስታ መግለጫ ሰልፎች በፀጥታና ደህንነት ተቋማት እንዲሁም በህብረተሰቡ ተሳትፎ በሠላም መከበራቸውን ተናግረዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል በያዝነው ሳምንት የኢሬቻ በዓል በቀጣይ ሳምንት ሕዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት የሚያከበራቸው በዓላት በመሆናቸው የፀጥታና ደህንነት ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው ወደ ተግባር መግባታቸውን ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ገልፀዋል፡፡ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት አማካኝነት በቴክኖሎጂ የታገዘ የቅድመ ወንጀል መከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
በዓላቱ ካለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ ሁሉም የፀጥታ አካላት አመራሮችና አባላት ኃላፊነታቸውን በተገቢው ሊወጡ እንደሚገባ የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው የፀጥታና ደህንነት ተቋማት በቅንጅት እና በጋራ መንፈስ ኃላፊነታቸውን በሚገባ በመወጣታቸው እንዲሁም የህብረተሰቡ ድጋፍ ታክሎበት የአዲስ አበባን ሠላምና ደህንነት በአስተማማኝ ደረጃ ማስጠበቅ እንደተቻለ ተናግረው በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄዱ ታላላቅ ሀገራዊና ህዝባዊ ኩነቶች እንዲሁም በዓላት በሠላም ማክበር የተቻለው ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰራ ማድረግ በመቻሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝና ለስኬታማ የፀጥታ ስራ የነዋሪውን አቅም በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የፖሊስ አመራሮችና አባላት እንደ ወትሮ ሁሉ ግዳጃቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እና ህብረተሰቡ ከተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች እራሱንና አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበት የጠቅላይ መምሪያው አዛዥ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሰዎች የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ ጥቆማ ለመስጠት በፌዴራል ፖሊስ አማካኝነት የለማውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ አፕሊኬሽን /EFP app/ እንዲሁም በፖሊስ ስልክ ቁጥሮች መጠቀም እንደሚችሉም አስታውቀው ለጋራ ደህንነት ሲባል በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ ፍተሻ ስለሚኖር የበዓሉ ታዳሚዎች ይህንኑ ተገንዝበው ለፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ የበዓላቱ አከባበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገልፀው በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የሚገኙ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በዓላቱን ምክንያት በማድረግ ከወትሮ በተለየ መልኩ በዓላቱ ተከብረው እስከሚጠናቀቁ ስምሪት ወስደው ወደ ተግባር መግባታቸውን በዚህም አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዓላቱ በሚከበርባቸው ቦታዎች በህገ መንግስቱ ዕውቅና የሌላቸው ህገ ወጥ እና የተከለከሉ ነገሮችን ይዞ መምጣት ክልክል እንደሆነ ርችት መተኮስ እና ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎች በምንም ዓይነት መልኩ መያዝም ሆነ መጠቀም እንደማይቻል ማሳሳቢያ ተላልፏል፡፡
በውይይቱ ላይ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ተግባር መግባታቸው እና ህብረተሰቡ ከፀጥታና ደህንነት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ የከተማውን ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑ ተገምግሟል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.