.png)
ሀሰተኛ ሰነዶችን በመኖሪያ ቤት ውስጥ በማዘጋጀት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመኖሪያ ቤት ውስጥ በማዘጋጀት የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እንዳስታወቀው÷ በተለያዩ አጋጣሚዎች ግለሰቦች የተሳሳተ ሰነድ በማዘጋጀት ወንጀል ላይ ይሳተፋሉ።
በዚህም ወደ ህገ ወጥ ድርጊት የሚገቡ ተጠርጣሪ ግለሠቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅሷል፡፡
በዛሬው እለትም በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የጎማ ቁጠባ ፖሊስ ጣቢያ በክፍለ ከተማው ወረዳ 7 ቀጠና 1 አካባቢ ሀሰተኛ ሠነዶችን እንደሚያዘጋጁ በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ጥናት አድርጓል።
ጥናቱን መነሻ በማድረግ የቤት መበርበሪያና የመያዣ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት በማውጣት ባደረገው ብርበራ መሰረት ተጠርጣሪዎቹ ሀሰተኛ መንጃ ፍቃድ፣ ፓስፖርት፣ የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የማንነት መታወቂያ ካርድ፣ የተሽከርካሪ ቦሎ፣ ደረሰኞችን ጨምሮ ሲያዘጋጁ እጅ ከፍንጅ መያዙን ገልጿል።
በተጨማሪም ሊሰሩ የተዘጋጁ ሀሰተኛ ሰነዶች የተያዙ ሲሆን ሰነዶቹን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው 1 ሺህ 18 የተለያዩ ማህተሞች፣ 1 ፕንሪተር፣ 1 የህትመት ማሽን፣ 2 ላፕቶፕ፣ 2 ስካነር፣ 1 አጉሊ መነፅር፣ 2 ማሸጊያ ማሽን፣ 8 ሲዲዎች፣ 1 መጠረዣ፣ 1 የፖስፖርት ማሽን እና 11 የማህተም መርገጫ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።
ህብረተሠቡ ሀሰተኛ ሰነዶችን መጠቀም በሀገር ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛና ትውልድ ገዳይ መሆኑን ተረድቶ መሰል ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ተሳትፎውን እንዲያጎለብት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጥሪ አስተላልፏል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.