.png)
"የህዝቡን የሠላም ባለቤትነት በማፅናት ለሀገርና ህዝብ ሠላም በጋራ ፀንተን እንፀልይ አበክረን እንስራ!"ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ
በመዲናችን በቅርቡ የሚከበረዉን የደመራና የመስቀል በዓል አስመልክቶ በከተማ ደረጃ የማጠቃለያ ዉይይት ተካሔደ
የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ ፣የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የማጠቃለያ የዉይይት መድረክ ነዉ።
በመርሀ ግብሩ ንግግር ያደረጉት አቡነ ህሪያቆስ የአዲስ አበባ የሀድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ የቦርድ ሰብስቢ እንደገለፁት የመስቀል በዓል የዓለም ሀጥያት የታጠበበት፤ሠላም በምድር ሠፍኖ አምላክና ሠዉ የታረቁበት ነዉ ብለዋል።
ይህ በዓል ለዘመናት በየዓመቱ በሀገራችን ስናከብር የድል በዓላችን የሚበሰርበት ታላቅ የሠላም፣የነፃነት፣የክብር እና የአብሮነት በዓላችን ስለሆነ በሠላም ፣በፍቅር ፣በአንድነት እና በድምቀት እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ በማለት አባታዊ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸዉ የዛሬዉን የመስቀል ደመራ በዓል ልዩ የሚያደርገዉ ሀገራችን የታላቁን ህዳሴ ግድብ በራስ አቅም አጠናቅቃ ድሏን በማጣጣም ላይ መሆኗን ጠቅሰዉ በዚህም በቀጠናችን የማይደፈር ሀገራዊ ቁመና መገንባት ችለናል ብለዋል።
በተመሳሳይም የበለፀገች ብዝሀነትን ማሳያ የሆኑ ሀይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላትን እሴታቸዉንና ትዉፊታቸዉን ጠብቀዉ ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መልኩ በድምቀት እንዲከበሩ መንግስት በጋራ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዉ ዛሬም ሀገራችን ብሎም ከተማችን የብዝሀ ምድር መሆኗን ለማስመስከር ሁሉም ሀይማኖቶች የሠላም ምሰሶና ጠበቃ በመሆናቸዉ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የጀመሩትን ዘላቂ አስተማማኝ የፀጥታ ስራ አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ በማለት ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸዉ እንደተናገሩት በዓለም በማይዳሰስ ቅርስ በዪኒስኮ የተመዘገበዉ ይህ ታላቅ ህዝባዊ በዓላችን የአንድነት ምልክት የሠላማዊ አብሮ የመኖር እና ብሔራዊ የማንነት ኩራት የቱሪዝም መስህብ ና የኢኮኖሚ ምንጭ በአጠቃላይ የዘርፈ ብዙ የባህላዊ እሴታችን ገፀበረከት ነዉ ብለዋል።
የዓለምን ትኩረት የሚስበዉ የመስቀል ደመራ በዓል በሠላም እንዲከበር የተቀናጀ ስራ ከከተማ አስተዳዳሩና ከሌሎች ተቋማት ጋር ሲሰራ መቆየቱን የጠቆሙት ዋና ፀኃፊዉ ሁላችንም ቀጣይ ትዉልድ ሊማርበት በሚችል መልኩ በድምቀት እንድናከብር በማለት መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋዉ የፀጥታና የደህንነት ሀይሉ ለበዓላትና ለሃይማኖቱ ተከታዮች ትልቅ ክብር በመስጠት በእኩል መንፈስ 24ሠዓት ፀንቶ በመስራት መንግስትና ህዝብ የጣለበትን ተልዕኮ በአግባቡ የተወጣበትና ዉጤታማ የሆነበት አሁንም ሆነ ወደፊት በተገኘዉ ልምድና ተሞክሮ በቂ ዝግጅት በመደረጉ የህግ የበላይነትን በማስፈን በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅ ተቀናጅቶ መስራቱ ይቀጥላል ብለዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.