
"ዘላቂ የሆነ የጤና አገልግሎት በመስጠት አምራች ኃይል እንፈጥራለን!" ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ::
በዛሬው እለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ካስገነባቸው 28 የጤና ፕሮጄክቶች መካከል 22 ጤና ጣቢያዎችን አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በመገኘት በከተማ አስተዳደሩ አዲስ የተገነቡ የወረዳ 11 እና 2 ጤና ጣቢያዎችን መርቀዋል።
በምርቃቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ሀላፊዎችና የክፍለ ከተማውና ወረዳ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ የከተማ አስተዳደሩ 15ሺ 960 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ እያስመረቀ መሆኑን ገልፀው የጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታል ግንባታዎች የሰው ተኮር ተግባራትን ላይ ትኩረት መደረጉንና የህዝቡን ጥያቄ በተግባር ለመመለስ የተሰራ ስራ መሆኑን መሳያ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባው አክለውም ዛሬ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከገነባናቸው 28 የጤና ፕሮጄክቶች መካከል በዛሬው እለት የተመረቁ 22 ጤና ጣቢያዎች በሆስፒታል ደረጃ ህክምና የመስጠት አቅም እንዲኖራቸው ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ በመሆናቸው አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ከተማ ለማድረግ የሚሰራውን ስራ እንደሚያጠናክሩ በመግለፅ ዘላቂና ዲጂታላይዝድ የሆነ የጤና አገልግሎት በመስጠት አምራች ህብረተሰብ እንፈጥራለን ሲሉ አስታውቀዋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ኒዕመተላህ ከበደ ከተማ አስተዳደሩ ከለውጡ ማግስት ለህብረተሰቡ ጥቅም የሚውሉና የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዛሬው እለት በክፍለ ከተማው የተመረቁ በሆስፒታል ደረጃ የህክምና ግብዓቶች የተሟሉላቸው 2 ጤና ጣቢያዎች ቃል በገባነው መሰረት የህዝባችንን ጥያቄ አንድ በአንድ እየመለስን መሆኑን ማሳያነው ሲሉ አስታውቀዋል።
በዛሬው የምርቃት መርሃግብር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ በክፍለ ከተማው የችግኝ ተከላ አካሒደዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.