በጀት ዓመቱ ከተማዋ በዘመናዊ የህክምና ታሪኳ የ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በጀት ዓመቱ ከተማዋ በዘመናዊ የህክምና ታሪኳ የነበራትን አቅም እጥፍ የሚያደርግ ስራ የተሰራበት መሆኑን ዶክተር ዮሀንስ ጫላ ገለፁ

በጀት ዓመቱ በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ የግንባታ ፕሮጀክቶች ከተማዋ በዘመናዊ የህክምና ታሪኳ የነበራትን አቅም እጥፍ ሊያደርግ የሚችል ስራ የተሰራበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሀንስ ጫላ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና የበጀት ዓመቱን ማጠቃለያ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሀንስ ጫላ ጤናን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በጤናው ዘርፍ ትልልቅ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ኃላፊው፣ በዘንድሮ በጀት ዓመት ፍትሃዊ ተደራሽነትን ከማስፈን አኳያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የመሆን አቅም ያላቸው አዳዲስ ጤና ጣቢያዎችን ስራ ለማስጀመር የህክምና መሳሪያዎች በመሟላት ላይ ይገኛል ብለዋል። 

በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ ከተማዋ በዘመናዊ የህክምና ታሪኳ የነበራትን አቅም እጥፍ ሊያደርግ የሚችል ስራ የተሰራበት አመት እንደሆነም ነው የገለጹት።

ነባር ሆስፒታሎችም ያላቸውን አቅም እጥፍ የሚጨምር ግንባታ ተከናውኗል ያሉት ኃላፊው፣  በማሳያነትም በራስ ደስታ፣ በዘውዲቱ መታሰቢያ፣ በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል እና በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የፎረንሲክ ህክምና ማዕከል የተገነባውን የማስፋፊያ ግንባታ ጠቅሰዋል።

የጤና ተቋማቱም በቅርብ ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ለህክምና ወደ ውጪ የሚሄዱ ታካሚዎችን በሀገር ውስጥ ህክምና ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ወደ ስራ ለመግባት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ከተማዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የመንግስት የጤና ተቋማትም የበኩላቸውን አስተዋፅዎ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.