.png)
#የጠሚሩምላሾች #PMOEthiopia
በአማራ ክልል የማህበረሰቡን የሰላም ሚና በተመለከተ
ማህበረሰቡ ሳይሸሽግ የታጠቁ አካላትን አትግደሉ፣ አትግደሉልኝ፣ እናንተም አትሙቱልኝ ማለት አለበት። ልጆቼን ፈተና እንዳይፈተኑ እንዳይማሩ አትከልክሉ፣ እንዳንሰራ አታድርጉ፣ ማዳበሪያ እንዳይመጣ አታድርጉ ማለት አለበት። ይህንን ሰሞኑን የአማራ ህዝብ በቅርቡ አሳይቷል፤ ሰላም ልማት እፈልጋለሁ ብሏል፤ በቃኝ ብሏል። ይህ ለሁሉም ግልፅ መልዕክት ነው። ለዚህ የህዝብ ጥያቄ የከበረ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ማንኛውም ሰው ወደ ስልጣን ሲመጣ ከዚህ ቀደም ምን ሰርተህ ታውቃለህ፣ ግብር ከፍለሃል ወይ፣ ማንን አገለገልክ፣ ታማኝ ነህ ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ህዝቡ ይህን እየጠየቀ ማጥራት አለበት። ማህበረሰቡ የሰላምና የብልሹ አሰራር ችግርን በዘለቂነት ለመፍታት ሚናውን መወጣት አለበት። ሰላም ሁልጊዜ የሚገነባ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ግጭቶች ተፈትተው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል። አንጻራዊ ሰላም ባይኖር ግብርናው፣ ማዕድኑ፣ ቱሪዝሙ አያድግም ነበር። አሁንም ቀሪ ችግሮችን በመፍታትና በጋራ በመስራት የሰላምን ዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል።
ትግራይ ክልልን በተመለከተ
የፕሪቶሪያ ስምምንት ለትግራይ ህዝብ እፎይታ አምጥቷል። የትግራይ ህዝብ ልጆቹን በየቀኑ ከማጣት ታድጓል። ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሌሎች ሀገራት ደግሞ መንግስት ሰላም ይሻላል ብሎ ለተዋጉት ኃይሎች እድል ይሰጣል የሚል አዲስ ባህል ፈጥሯል። በክልሉ አገልግሎትን በሚመለከት ቴሌኮም፣ ባንኮች፣ አየር መንገድና ሌሎችም አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ጀምረዋል። የተፈናቀሉ ሰዎችን በመሚመለከት ራያ መቶ በመቶ ጸለምትም ተመልሰዋል። ቀሪ ወልቃይት ያልተመለሱ አሉ፤ መንግስት ያልምተመለሱ ተፋናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የጸና አቋም ነው ያለው። የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋምና ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀልም በፍጥነት መፈጸም አለበት። ይህ ጥቅሙ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጭምር ነው። የፌደራል መንግስት ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በሰላም የመፍታት ፅኑ አቋሙን በተደጋጋሚ አሳይቷል። የትግራይ ህዝብ ጦርነት ፈጽሞ አይፈልግም። ሆኖም የዓለምን ሁኔታና የዘመኑን ውጊያ ባለመገንዘብ፣ መንግስት በተለለያዩ ችግሮች ተወሯል፤ የሚያገዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን ነው በሚል ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ አሉ። ይህ የተሳሳተ አካሄድ ነው ትግራይ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ችገሮችን በውይይት በንግግር መፍታት ነው። የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ ጦርነት እንዳይገባ አሁኑኑ የሰላም ሚናችሁን ተወጡ። መንግስት አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለውም። ማልመት ነው ፍላጎታችን። ሁሉም ህዝብ ማወቅ ያለበት ጦርነት አያስፈልግም። ትግራይ ክልልን ጨምሮ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሚና ማበርከት አስፈላጊ ነው።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ውጭ ህልውና የላትም። ከኢትዮጵያ ውጭ ጎረቤቶቻችን ህልውና የላቸውም። ያልተፈቱ ችግሮች ስለነበሩ በዚያ ምክንያት ወጣ ገባ የሚሉ ጉዳዮች አሉ። እኛ መልካም ዘር መዝራት ነው ፍላጎታችን። የባህር በር ፍላጎታችን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ማግኘት እንጂ በኃይል አንፈልግም። በሰላማዊ መንገድ ነው ሁሉንም ማሳካት የምንፈልገው። ሉዓላዊነታቸውን እናከብራለን። ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት፤ ይህ ሙሉ እንዲሆን ደግሞ የባህር በር እንድታገኝ ጎረቤቶቻችን በጎ ምላሽ መስጠት አለባቸው። ኢትዮጵያ በትናንሽ ጠጠር አትታወክም፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ትልቅ ባህር ናት። ኢትዮጵያ የሚያውካትን ተከላክላ መልማት ትችላለች። ይህንን በደንብ ተገንዝቦ ሰብሰብ ማለት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚ፣ የህዝብ ቁጥር፣ የዘመነ ሰራዊት ያላት ሀገር ናት። ከኤርትራ ጋር የጦርነት ስጋት ለሚያነሱ አካላት በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ውጊያ እንደማንፈልግ ማወቅ ይገባል፤ ይህንን በእነሱም በኩል ማድረግ አለባቸው። ባለፉት ሰባት ዓመታት አንድም ግጭት ከጎረቤት ሀገራት ጋር አላደረግንም። ትብብር አብሮ ማደግ ነው ፍላጎታችን። የማንሰራራት ጉዟችን እንዳይስተጓጎል ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር በሰላም መኖር እንፈልጋለን። ሰላማችንን የሚያሰጋ ነገር ካለ ግን ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም አላት። ትበለፅጋለች። ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች፤ ኢትዮጵያ ትጸናለች፤ ለማጽናት የሚያበቃ በቂ አቅም አላት፤ ኢትዮጵያ በታሪክ ጠላቶች ነበሯት አሏት፤ አይናቸው እያየ ግን እናንሰራራለን።
የመሃሉ ዘመን ወጥመድን በተመለከተ
የመሃል ዘመን ማለት በሽግግሩ ማጠናቀቂያና በጸናው ስርዓት መጀመሪያ ላይ ማለት ነው። ስድስት ዓመታት የፖለቲካ ሪፎርም አደረግን የሰፈር ፓርቲ አጥፍተን ብልጽግናን ፈጠርን፡ በየሰፈሩ የነበረን ፓርቲ አምጥተን ብልጽግናን መፍጠር በራሱ ትልቅ እምርታ ነው። እኛ ያደረግነውን እኮ ብዙዎቹ አልቻሉም ገና በማህበራዊ ድረ ገጽ ውስጥ ነው ያሉት። ከተቋማት ሪፎርም ጀምሮ የተሟላ ኢኮኖሚ ሪፎርም ስላደረግን ነው መሃል ያልነው። ይሄ ማለት ሽግግሩም መቶ በመቶ አልጠፋም የጸናውም መቶ በመቶ አልጀመረም። መሃል ላይ ነው ያለነው። ያኛው እያለቀ ይህኛው እየጀመረ ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ብዙ ድካሞች አሉ። የለውጥ ድካም የሚጀምረው መሃል ላይ ነው። መጀመሪያ ሁሉም ጉልበት አለው በኋላ ያለው ነገር የሚጨበጥ የሚነካ ይሆናል። ለምንድን ነው የመሃሉ ዘመን የሚያመጣብንን ፈተና እንጠንቀቅ ያልነው ብዙ ፈተና አይተናል። ብዙ ድል አግኝተናል፤ እኛ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የሰራናቸው ስራዎች ላለፉት ሀምሳ እና ስልሳ ዓመታት አልተሰሩም ተጨባጭ ለውጥ አለ ኢትዮጵያ ውስጥ። ይህ ግን እንዳያኩራራን መድረስ የሚገባን ቦታ ሳንደርስ አንቆ እንዳያስቀረን አልቀን እንድንሰራ ፈተናን እንዳንለማመድ ድልን ደግሞ ማቀብና መጠበቅ እንድንችል ነው። መሃል ወደ ፊትም መስፈንጠር ያስችላል፤ ወደኋላም እንደገና ሊያንሸራትተን ይችላል ። ለዚህ ነው ነቅተን የመሃሉ እስረኛ እንዳንሆን ያልነው። ከዘመን ጋር የምንዘምን፣ ዘመንን የምንዋጅ፣ አብረን እንድናድግ፣ ባለንበት እንዳንቆም ካስፈለገ የመሃሉ ዘመን ፈተናን መገንዘብ ያስፈልጋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.