
#የጠሚሩምላሾች #PMOEthiopia
የማህበረሰቡን የሰላም ሚና በተመለከተ
ማህበረሰቡ ሳይሸሽግ የታጠቁ አካላትን አትግደሉ፣ አትግደሉልኝ፣ እናንተም አትሙቱልኝ ማለት አለበት። ልጆቼን ፈተና እንዳይፈተኑ እንዳይማሩ አትከልክሉ፣ እንዳንሰራ አታድርጉ፣ ማዳበሪያ እንዳይመጣ አታድርጉ ማለት አለበት። ይህንን ሰሞኑን የአማራ ህዝብ በቅርቡ አሳይቷል፤ ሰላም ልማት እፈልጋለሁ ብሏል፤ በቃኝ ብሏል። ይህ ለሁሉም ግልፅ መልዕክት ነው። ለዚህ የህዝብ ጥያቄ የከበረ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ማንኛውም ሰው ወደ ስልጣን ሲመጣ ከዚህ ቀደም ምን ሰርተህ ታውቃለህ፣ ግብር ከፍለሃል ወይ፣ ማንን አገለገልክ፣ ታማኝ ነህ ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ህዝቡ ይህን እየጠየቀ ማጥራት አለበት። ማህበረሰቡ የሰላምና የብልሹ አሰራር ችግርን በዘለቂነት ለመፍታት ሚናውን መወጣት አለበት። ሰላም ሁልጊዜ የሚገነባ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ግጭቶች ተፈትተው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል። አንጻራዊ ሰላም ባይኖር ግብርናው፣ ማዕድኑ፣ ቱሪዝሙ አያድግም ነበር። አሁንም ቀሪ ችግሮችን በመፍታትና በጋራ በመስራት የሰላምን ዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል።
ሰላምና ጸጥታን በተመለከተ
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የጸጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት ነው። አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የስንፍና ፖለቲካ የወለደው ችግር ነው። የስንፍና ፖለቲካ በሀገራችን ተንሰራፍቷል። በዚያ ምክንያት ግጭት ጠብ፣ ተቃርኖን ይወልዳል። ስራ አያውቁም ስራ አይወዱም ስራ አይሰሩም። አንድ ሰው ስራ ካልሰራ ደግሞ አልተማረም ማለት ነው። በስራ ተመንዝሮ የሚገኝ እውቀትና ልምድ ነው ሰውን አዋቂ የሚያሰኘው። በእኛ ሀገር አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር ላብ አደር አለ፤ አሁን ደግሞ አውርቶ አደር ተጨምሯል። አውርቶ አደር ካላጋጩ ገቢ አያገኙም። እነዚህ ሰነፍ ፖለቲከኞች ስራ ሳይሰሩ፣ አገልግሎት ሳይሰጡ መብላት የሚፈልጉ ናቸው። ሁለተኛው መንስኤ የኃይል ፖለቲካ ነው። ክላሽ ካነገትኩ ፍላጎቴ ይሳካል ብለው የሚያምኑ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይልና በወሬ እናፈርሳለን ብለው የሚያምኑ፣ በመግደል መሸነፍ እንጂ ማሸነፍ እንደሌለ የማያምኑ ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት አትማሩ፣ ማዳበሪያ አትውሰዱ ብለው ሰዎችን የሚገድሉ ሰዎች ካሉ ይህ እኩይ አላማ ነው። ግድያ ሽንፈት ብቻ ነው የሚያመጣው ብሎ ማመን ያስፈልጋል። መቆም አለበት። ሶስተኛው ገፊ ምክንያት ድህነት ነው፤ ድሀነትን ካልቀነስን ስራ ካልፈጠርን ችግሩን መቅረፍ ያስቸግራል። ኋላቀርነት እና ዘረኝነት አባባሽ ችግሮች ናቸው። ዘረኝነት ሌላው ስር የሰደደ ችግር ነው። ዘረኝነት ልኩን ሲስት ለሰው ልጅ ጠንቅ ይሆናል። እነዚህ እሳቤዎች የውጭ ጣልቃ ገብነት ታክሎበት የባንዳነት ስሪት ደግሞ በመስፋቱ ችግሩን አባብሶታል። ኢትዮጵያ ስትጋጭ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ እሳት ጫሪ ጥልፊቶች አሉ። ኢትዮጵያውያንም እሳት ጫሪዎችን ማወቅና ማረም ያስፈልገናል። ያን ጊዜ ችግሩ ይፈታል።
#የጠሚሩምላሾች
#PMOEthiopia
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.