
በአዲስ አበባ ከተማ የ2017 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 95 % ያህሉ 50% እና ከዛ በላይ በማምጣት ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ መሸጋገራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ አስታወቁ።
ኃላፊው በዛሬው እለት የ2017 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን በማስመልከት ለተለያዩ የመንግስትና የግል የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት በየአመቱ አበረታች ውጤት ማሳየት ላይ መሆኑን ኃላፊው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው ጠቁመው በ2017 ዓ.ም ፈተናውን ከወሰዱ 79,034 ተማሪዎች መካከል 75,085 ተማሪዎች ማለትም 95 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች 50% እና በላይ አስመዝግበው ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል።
ዶክተር ዘላለም አያይዘውም የ2017 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ፈተና ውጤታማ እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ሴክተሩ ትኩረት በመስጠት የትምህርት ቤት ምገባን ጨምሮ የደንብ ልብስ እና ሌሎች ተጨማሪ የትምህርት ግብአቶች ማቅረቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው በየትምህርት ቤቱ የማጠናከሪያ ትምህርትን ጨምሮ ተማሪዎች በቴሌቪዥን የሚማሩበት አማራጭ መመቻቸቱ እና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራታቸው ለውጤቱ መገኘት ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን አመላክተዋል።
ዘንድሮው በከተማ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ከ1 እስከ 4 የሚሆኑት ከመንግስት ትምህርት ቤቶች መሆናቸው በግልና በመንግስት ትምህርት ቤቶች መካከል ያለዉን የውጤት ልዩነት እጅግ እየተቀራረበ መምጣቱን ኃላፊው በመግለጫቸው ጠቁመው መምህራንን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተማሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ከታች የተቀመጠውን ሊንክ በመጠቀም ከዛሬ ጀምሮ ውጤታቸውን ማየት እንደሚችሉ በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁሟል።
Telegram bot; @emacs_ministry_result_qmt_bot
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.