.png)
ዛሬ በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ በተለምዶ "ፓስተር አደባባይ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የዘመሙ እና ደሳሳ የቀበሌ ቤቶችን አፍርሰን ለአካባቢው ነዋሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ህንፃ መኖሪያ ገንብተን አስተላልፈናል።
ይህ አካባቢ እጅግ በጣም የቆሸሸ፣ ቤቶቹም የወዳደቁ ሲሆኑ የዛሬ ሶስት ዓመት አካባቢውን ማልማት ስንጀምር ገብተን ለመስራት የተቸገርን ቢሆንም የዛሬውን ጨምሮ ቀድመን የገነባናቸው በጠቅላላ አምስት የመኖሪያ ህንፃዎች አካባቢውን ከመቀየር በተጨማሪ በውስጣቸው መንገድ፣ የህፃናት መጫዎቻ፣ የህፃናት ማቆያ፣ ዘመናዊ የመጸዳጃና የማብሰያ ቦታዎች፣ እንዲሁም የጋራ መገልገያ ስፍራዎች ተካትተው የተገነቡ ናቸው።
ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮችን ገንብተን ለነዋሪዎች ስናስተላልፍ አካባቢውን ንፁህ እና ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ ነዋሪዎቻቸው ዘመናዊ አናኗር እና ጤናማ ኑሮ ለማረጋገጥ ሲሆን አካባቢውን ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ለመቀየር በያዝነው እቅድ መሠረት ዛሬም ሁለት አዳዲስ ህንፃዎችን አስጀምረናል::
የሚፈሱ እምባዎችን እያበስን፣ የዘመሙ ጎጆዎችን እያቃናን እና ቆሻሻን እያፀዳን ለነዋሪዎቻችን ምቹ አካባቢን በመፍጠር እንዲሁም በከተማችን ያሉ ትውስታዎችን እና ቅርሶቻችንን አድሰን የቱሪስት መዳረሽ በማድረግ ለከተማችን ተጨማሪ ገቢ፣ የስራ እድል እና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራን ነዉ።
ስራው በመንግስት አቅም ብቻ የሚከናወን አለመሆኑን በመረዳት ጥሪያችንን ተቀብለው ከጎናችን የቆሙ ልበ ቀና ባለጸጎቻችንን በነዋሪዎቻችን ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ::
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.